ማህበሩ ሀገርን ለማዳን ለሚደረገው የህልውና ዘመቻ ድጋፍ አደረገ

Published by corporate communication on

ሁለተኛ ቀኑን የያዘው 7ኛው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር የምክር ቤት አባላት ጉባኤ ሀገርን ለማዳን ለሚደረገው የህልውና ዘመቻ የ2 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ እንዲደረግ ወሰነ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ አጋርነታቸውን ለማሳየት ከማህበሩ ሂሳብ ወጪ የሚሆን የ2 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ እንዲደረግ ወስነዋል፡፡

ማህበሩ የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ሲከፈል እንደአዲስ የተቋቋመና የአቅም ውስንነት ያለው ቢሆንም ከሀገር የሚበልጥ የለም በሚል ድጋፉን ለመስጠት መወሰኑ በጉባዔው ላይ ተገልጿል፡፡

በቀጣይም በሚቻለው ሁሉ አባላቱን በማስተባበር በተለያዩ መልኮች ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል የጋራ መግባባት ተደርሷል፡፡

ማህበሩ በትላንት ውሎው የመሰረታዊ ሠራተኛ ማህበሩ ሊቀ መንበር አቶ መኮንን ክፍሌ ያቀረቡትን የ2013 በጀት ዓመት ክንውን ሪፖርት፣ የማህበሩን የኦዲት ሪፖርት፣ የሂሳብ ሪፖርት  እና የማህበሩ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድና በጀት ላይ ውይይት አድርጎ አጽድቆታል፡፡

በዛሬው ዕለትም ከፌደራል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ስለተሻሻለው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ እና ስለሰራተኛ መብቶች እና ግዴታዎች ለምክር ቤቱ አባላት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በነገው ዕለት ከተቋሙ ከፍተኛ የስራ አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ ጉባኤው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

4 − 2 =