ሚኒስትሩ የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን ጎበኙ

የውሃ፣መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ከቬራ ሶንግዌ ጋር በመሆን የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታንና በሥራ ላይ የሚገኘውን ጊቤ ሶስት የውሃ ኃይል ማመንጫን ጎበኙ፡፡
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ያሏትን የውሃ ሃብቶች ለዘላቂ እድገትና ለዜጎች ህይወት መሻሻል እንዴት በአግባቡ እየተጠቀመች እንደሆነ ለማየት አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
“በኦሞ ወንዝ ላይ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረጋችን በተመሳሳይ ሌሎች ወንዞቻችንንም እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደምንችል ማሳያ ነው ብለዋል” ሚኒስትሩ፡፡
ጊቤ ሶስት የውሃ ኃይል ማመንጫ በአሁኑ ሰዓት 1870 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው ላይ ሲሆን አሁን ግንባታው 39 በመቶ የደረሰው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ደግሞ ሲጠናቀቅ ደግሞ 2160 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያመነጭ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
“የኮይሻና የሕዳሴ ግድቦች ሲጠናቀቁ አሁን ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት በ170% በማሳደግ በ2022 ሙሉ በሙሉ ለዜጎች ኃይል ለማቅረብ በምናደርገው ጥረት ላይ ትልቁን ሚና ይጫወታሉ” ማለታቸውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሽን ዘግቧል።
በጉብኝቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ተገኝተዋል።
0 Comments