ሙስናን እና ሌብነትን በተደራጀ መልኩ መከላከል እንደሚገባ ተገለፀ

Published by corporate communication on

ሙስና የሀገርን ዕድገት በማቀጨጭ ህዝቦችን ለድህነት የሚዳርግ በመሆኑ በፅኑ መታገል  እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ስራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ተናገሩ።

ለተቋሙ አመራሮች በስነምግባር እሴቶች ላይ የተዘጋጀው ስልጠና በንግግር ሲከፍቱ  የጽ/ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መርጋ ተረፈ  እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በዓመት ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ በሙስና ይባክናል።

ይህንንም በጊዜ መከላከል ካልተቻለ በሀገር ላይ  ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል ብለዋል፡፡

ሥራ አስፈፃሚው እንደገለፁት ሙስና የፍትህ ስርዓትን በማዛባት፣የፖለቲካ ስርዓትን በማበላሸት ሀገርን ለሁለንተናዊ አደጋ የሚያጋልጥ ካንሰር ነው፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት የፌደራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ከፋለ በበኩላቸው ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የተቋሙ አመራሮች አርአያ በመሆን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የስካንዲቪያን አገሮች የሆኑት እንደ ስዊድን እና ኖርዌይ ዜጎችን በስነ ምግባር በማነፅ አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑን የገለፁት አቶ ተስፋዬ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ ከአመራር ጀምሮ በሙስና ስር የሰደደ ችግር ያለባቸው ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ የተደራጀ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ተስፋፍቶ እንደነበርና ይህም ሔዶ ሔዶ ሀገራዊ ትርምስ መፍጠሩንና የመንግስት ለውጥ ማስከተሉን ከፍተኛ ባለሙያው እንደማሳያ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት ተቋም እንደመሆኑ አደረጃጀቱን በማዘመንና የሙስና በሮችን በመዝጋት የተጣለበትን የህዝብ አደራ በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ተቋም የሚታይን ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማክሰም አሳሪ የሆኑ መመሪያዎችን ማስተካከል፤ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር ስርዓት ማጎልበት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

አቶ ተስፋዬ እንዳሉት የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘገቡ ማድረግ አንዱ የሙስናና ብልሹ አሰራር መቆጣጠሪያ መንገድ ነው፡፡

በተቋሙ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ የስራ ክፍሎችን በመለየት በትኩረት በመደገፍና በመከታተል በግዥ ስርዓት፣ በቅጥር እና በአገልግሎት አሰጣጥ ከአድሎ የፀዳ፣ እኩልነትንና ፍትሐዊነትን ያማከለ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባ ከፍተኛ ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

one × one =