መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስኬታማ ስራ አከናውኛለው አለ

Published by corporate communication on

የተቋሙን ውጤታማነት እና ምርታማነት ባማከለ መልኩ የሠራተኛውን ጥቅም ለማስከበር የሚያስችሉ ስኬታማ ሥራዎች ማከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር አስታወቀ፡፡

የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ መኮንን ክፍሌ እንደተናገሩት ቀደም ሲል እስከ አንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ ጊዜ ይወስድ የነበረውን የደረጃ ዕድገትና ዝውውር ከተቋሙ አመራሮች ጋር በቅንጅት በመስራትና አሠራሩን በማዘመን ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡

የተቋሙን ሴት ሠራተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት በቅጥር፣ በደረጃ ዕድገትና ዝውውር እንዲሁም በትምህርት ዕድል ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መመሪያዎች ተግባራዊ መደረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለህክምና ከሚወጣው ወጪ 10 በመቶ ያህሉ ከሠራተኞች የሚሸፈን መሆኑን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ የስኳር፣ የኤችአይቪ፣ የልብህመም እና የደም ግፊት ህመሞች ወጪያቸው መቶ በመቶ በተቋሙ እንዲሸፈን መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የዘርፍ ማህበራትን ከማጠናከር አኳያም የስራ አስፈፃሚና የኦዲት ኮሚቴ አባላትን ያካተተ  የመስክ ስምሪት በማከናወን የተጓደሉ የዘርፍ አመራሮች እንዲሟሉ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከማህበር አባላት ጋርም ሰፊ ውይይት በማድረግ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከማህበር አባላት የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ከየዘርፉ የሥራ አመራሮች ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የተቋሙን አፈፃፀም ለማሳደግና የሠራተኛውን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከተቋሙ የሥራ አመራሮች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የሠራተኛው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ የሚችለው የተቋሙ ውጤታማነትም ሲያድግ በመሆኑ ሁሉም ሠራተኞች ለተቋሙ ዕድገት እና ብልፅግና በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ሊቀመንበሩ አሳስበዋል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

9 − seven =