ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች የኃይል አቅርቦት ስምምነት ተፈራረመ

Published by corporate communication on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ለተገነቡት የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት መሰረተ ልማት ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ከሁለት የቻይና ኩባንያዎች ጋር ተፈራረመ፡፡

ሲኖ ሀይድሮ እና ሲዩአን ኤሌክትሪክ (sieyuan electric CO. LTD) ከተሰኙ ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ጋር መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈረመው ስምምነት ለቡሬ፣ ለበአከር፣ የወይናንታ እና የገንዳ አርባ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ለዳንሻ፣ ሁመራ፣ ጎንደር II ማከፋፈያ ጣቢያዎች የዲዛይን፣ የዕቃዎችን ፍብረካና አቅርቦት፣ የግንባታ እንዲሁም የሙከራና ፍተሻ ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡

የፊርማ ስነ-ስርዓቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የየኩባንያዎቹ ተወካዮች ተፈራርመዋል፡፡

አቶ አሸብር ባልቻ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት መንግስት የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ስምምነቱ ለኢንዱስትሪ ፓርኮቹን የኃይል ጥያቄ ለመፍታት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቶችን ግንባታ በተቀመጠላቸው መርሃ ግብር መሰረት ለማጠናቀቅ ኩባንያዎች ሌት ተቀን መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

ተቋሙ ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ከወሰን ማስከበር ነፃ ከማድረግ ጀምሮ ለኩባንያዎች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

የኩባንያዎቹ ተወካዮች በበኩላቸው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በተለያዩ የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ፕሮጀክቶችን በመገንባትና ዕቃ በማቅረብ ተሳትፎ እንደነበራቸው አስታውሰው በስምምነቱ መሰረት የፕሮጀክቶችን ሥራ በጥራትና በተቀመጠላቸው መርሃ ግብር  መሰረት አጠናቆ ለማስረከብ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ኩባንያዎቹ በቀጣይ ከተቋሙ ጋር አብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡

በግዥ መምሪያ የፕሮጀክት ግዥ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሁሴን አደም በበኩላቸው እንደገለጹት ከሲዩአን ኤሌክትሪክ ኩባንያ ጋር የተካሄደው ስምምነት ባለ 230 ኪሎ ቮልት የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማከፋፈያ ጣቢያ የዲዛይን፣ የዕቃ ማምረትና አቅርቦት፣ የግንባታ፣ የሙከራና ፍተሸ ስራዎችን ለማከናወን እንዲሁም ለጎንደር II ባለ 230 ኪሎ ቮልትና ለሁመራ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማሻሻያ ስራ እና አዲስ ለሚገነቡት ለበአከርና ዳንሻ ባለ 230/33 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ የሚያገለገሉ ዕቃዎችን ለማቅረብ ነው፡፡

የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክትን በ14 ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለማስረከብ እና ከ15 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይና ከ118 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አቶ ሁሴን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሁሴን አክለውም ለጎንደር II፣ ለዳንሻ፣ ለበአከርና ለሁመራ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ የሚዉለውን ዕቃ ለማቅረብ የተካሄደው ስምምነት ከ10 ነጥብ 8 ሚሊዬን ዶላር በላይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ ከሲኖ ሀይድሮ ኩባንያ ጋር የተካሄደው ስምምነት በምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ አካባቢ ለሚገነባው የገንዳ አርባ እና በይርጋለም አካባቢ ለተገነባው የወይናንታ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርክ ባለ 132/33 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ የዲዛይን፣ የፍብረካና አቅርቦት፣ የግንባታ እንዲሁም የሙከራና የፍተሻ ስራዎችን ለማከናወን ነው፡፡

የገንዳ አርባንና የወይናንታን የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ፕሮጀክት በ12 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እና ለዚህም ከ13 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላርና ከ14 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ስምምነት መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

ለሁሉም ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

two × five =