ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል ለማቅረብ እየተሰራ ነው

Published by corporate communication on

ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለፁት ለምርቃት ዝግጁ ለሆነው ለቡሬ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ሁለት አማራጮች ተይዘው ጥናት ሲካሔድባቸው ቆይተዋል፡፡

ለፓርኩ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ከባህርዳር ማከፋፈያ ጣቢያ በዳንግላ- ቡሬ በኩል 69 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ባለ 132 ኪሎ ቮልት መስመር እንዲሁም ከደብረ-ማርቆስ ማከፋፈያ ጣቢያ ወደ ፓርኩ የሚሄድ 92 ኪሎ ሜትር ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር የመዘርጋት አማራጮች ተለይተው የቴክኒክና የፋይናንስ ትንተና እንደተካሄደባቸው ገልፀዋል፡፡

በተደረገው የቴክኒክና የፋይናንስ ትንተና መሠረት ከባህርዳር-ዳንግላ እንዲመጣ የታሰበው የማስተላለፊያ መስመር ባለ 132 ኪሎ ቮልት በመሆኑ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር የኃይል መዋዠቅ ሊያጋጥም እንደሚችል አመልክቷል፡፡ 

በዚህም ምክንያት ከደብረ-ማርቆስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ጀምሮ እስከ ቡሬ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና የማከፋፈያ ጣቢያ ለመገንባት መታቀዱን ነው አቶ ሞገስ ያብራሩት፡፡

ፕሮጀክቱን ለማከናወን ዓለምአቀፍ ጨረታ እንዲወጣ ተደርጓል ያሉት ኃላፊው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን እና የማከፋፈያ ጣቢያውን ገንብተው ለማስረከብ ብቃት ያላቸው ሥራ ተቋራጮች እስከ የካቲት 05 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ክፍት በተደረገው ጨረታ ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ የወሰን ማስከበር ጉዳይ ለፕሮጀክት ግንባታ መጓተት ምክንያት እንዳይሆን ከወዲሁ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በመንግሥትና የግል አጋርነት ይገነባሉ ተብለው ከተለዩት መካከል አንዱ እንደነበር የጠቆሙት ኃላፊው በተለያዩ ምክንያቶች ዕውን ሊሆን አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡ ለቡሬ፣ ለቡልቡላ፣ ለባከርና ለይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል ለማቅረብ አሸናፊው ተቋራጭ ከተለየ በኋላ ፕሮጀክቱን በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

fourteen + 18 =