ለዳያስፖራው ማህበረሰብ ምቹ የድጋፍ ማድረጊያ ዌብሳይትና የሞባይል መተግበሪያ እየተዘጋጀ ነው

Published by corporate communication on

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የገንዘብ ማሰባሰቢያ የሚያገለግል ዌብሳይትን መሠረት ያደረገ የገንዘብ ማስተላለፊያ ሶፍትዌርና የሞባይል መተግበሪያ ተሰርቶ በሥራ ላይ ሊውል መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ አስተዳደር መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ መንግሥቱ  አስታወቁ፡፡

ዌብሳይትን መሠረት ያደረገ የገንዘብ ማስተላለፊያ ሶፍትዌሩ እየበለፀገ ያለው ቻፓ ሶሊዩሽን ኮርፖሬሽን  በተባለ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋም ሲሆን የሞባይል መተግበሪው ደግሞ በለንደን በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጎ ፍቃደኞች የበለፀገ ነው፡፡

ቻፓ ሶሊዩሽን ኮርፖሬሽን ከአንድ ሃገር ወደ ሌላ ሃገር በሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች ውስጥ ገንዘብ ነክ የይለፍ ሥርዓቶችን ለማመቻቸት እንደተቋቋመ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከቦንድ ግዢ ባሻገር ግድቡን በገንዘብ መርዳት እንደሚፈልጉ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ እስካሁን በስጦታ መልክ ገንዘብ ለመርዳት የሚያስችሉ ቀላል መንገዶች እንዳልነበሩ አለመኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ግን ዲያስፖራው ቆንስላ ጽ/ቤት ድረስ መጓዝ ሳይጠበቅበት ጊዜ እና ገንዘቡን ቆጥቦ በተዘጋጀው ሲስተም ኢንተርኔትን በመጠቀም ብቻ መገልገል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ለህዳሴ ግድብ ገንዘብ ማሰባሰቢያ እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ሲስተም በመሆኑ ግድቡ የኔ ነው የሚል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ሲስተሙን በመጠቀም ግድቡን እንዲደግፍ ያስችለዋል ብለዋል፡፡

የበለፀገው ዌብሳይትና የሞባይል መተግበሪያ የግድቡን ግንባታ በስጦታ መልክ በገንዘብ ለማገዝ ከመርዳቱም ባሻገር የውጭ ምንዛሬ አቅምን ለማጎልበት ከማስቻሉም በተጨማሪ ህዝቡ ከግድቡ ጎን መሰለፉን ማረጋገጫ መንገድም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዌብሳይትን መሰረት ያደረገው ይህ ሶፍትዌር ከገንዘብ ማስተላለፊያ መንገድነቱ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ እንዲከታተሉ ጭምር መረጃዎችን ለማግኘት ይረዳቸዋልም ሲሉ አቶ አለማየሁ ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኞች የተዘጋጀው ይህ የገንዘብ ማስተላለፊያ ሲስተም ለግድቡ ግንባታ መፋጠን ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

two × two =