ለዓመታት የቆመው የጢስ አባይ 2 ኃይል ማመንጫ አንድ ዩኒት በተቋሙ ባለሙያዎች ተጠግኖ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል

Published by corporate communication on

ከሰባት ዓመታት በላይ በብልሽት ምክንያት የቆመውን የጢስ አባይ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ አንድ ዩኒት ሥራ ለማስጀመር የሚያስችሉ ጥገና በተቋሙ ባለሙያዎች እየተከናወነ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ጉታ አስታወቁ፡፡

ዩኒቱ በደለል ስለተሞላና የተርባይን ሻፍት ዝንፈት ስላጋጠመው ተርባይኖቹ መንቀሳቀስ እንዳቆሙ በጥናት መታወቁን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ ችግሩን አስተካክሎ ዩኒቱን ሥራ ለማስጀመር በተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መጠየቁን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የተቋሙ ባለሙያዎች በኃላፊነት ስሜት በመንቀሳቀሳቸው በበጋው ወራት ደለሉን የማስወገድና ተርባይኑን የማንቀሳቀስ ሥራ ተከናውኖ አሁን የጥገና ሥራው ተጀምሯል ብለዋል፡፡

የጥገና ቡድኑ መሪና የፊንጫ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሹመት በላቸው በበኩላቸው የጥገና ሥራው ከተጀመረ በኋላ የተርባይን ሻፍት ዝንፈትን የማስተካከል፣ ዩኒቱ እንዲሰራ ለማድረግ ተሸከርካሪ አካሉን ወይም ሮተር ከፍ የማድረግ (Lifting Pump)፣ የተርባይኑ  ተሸከርካሪ አካል የማስተካከል ሥራዎች (Trust bearing) መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡

ለዓመታት የቆመውን ተርባይን ማሽከርከር መቻሉ ዩኒቱን ሥራ ለማስጀመር መቃረባችን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቱን ሥራ ለማስጀመር የሚቀረው ሥራ የተቃጠለውን የጀነሬተር ስቴተር ዋይንዲንግ በሌላ በመተካት የሙከራና ፍተሻ ሥራ ማከናወን ብቻ እንደሆነ አቶ ሹመት ተናግረዋል፤ ይህም ከአንድ ወር ያላነሰ ጊዜ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኃላፊዎቹ እንዳሉት እንዲህ ዓይነት ለረጅም ዓመታት ያልተንቀሳቀሰ ዩኒትን በተቋሙ ባለሙያዎች የመጠገን ሥራ ሲከናወን የአሁኑ የመጀመሪያው ነው፡፡

በጥገና ሥራው ላይ የተሳተፈችው ብቸኛዋ ሴት የጣቢያው የጥገና ባለሙያ ኸደም መሐመድ ደግሞ ሥራው ብዙ ልምድ ያገኘችበት እንደሆነ ትገልፃለች፡፡

ዩኒቱን ወደ ሥራ ማስገባት ለርስዋም፣ ለጥገና ቡድኑም ለተቋሙም ትልቅ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው እንደሆነ ተናግራለች፡፡

ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ለተግባር ልምምድ ተመድበው ከመጡት ስድስት ተማሪዎች መካከል የአራተኛ ዓመት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ተማሪ ይብለጥ በሪሁን እየተሳተፈበት ያለው የጥገና ሥራ ንድፈሐሳብን በተግባር የተረጎምንበት ነው ብሎታል፡፡

የጥገና ሥራው በስኬት ከተጠናቀቀ ዩኒቱ እስከ 33 ሜጋዋት ኃይል ማመንጨት ይችላል፡፡

የጢስ አባይ 2 የውኃ ኃይል ማመንጫ ሥራ የጀመረው በ1993 ሲሆን 72 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ተገነባ ጣቢያ ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

10 − 7 =