ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያ ለመገንባት የሚያስችል የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ተካሔደ

Published by corporate communication on

ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያ ለመገንባት የሚያስችል የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት በስካይ ላይት ሆቴል ተካሔደ። የግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ- ሥርዓቱ የተካሄደው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ካርዲናል ኢንደስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በጋራ ለመስራት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ ነው።በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ተደራሽነት ለማሳደግ የሚቻለው  የኃይል መሙያ ጣቢያ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት መሆኑን ነው አቶ አሸብር የገለፁት።ተቋሙ መቶ በመቶ የአረንጓዴ ኢነርጂ ፖሊሲን በመተግበር ኤሌክትሪክ እያመነጨ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሥራ አስፈፃሚው በሀገሪቱ ከ180 በላይ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች  ያሉት በመሆኑ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅርበት በመስራት ኢንዱስትሪውን ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋሙ በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት የሚያስችሉትን ቅድመ ዝግጅቶች አጠናቋል።በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ እንደተናገሩት ኢነርጂ ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።በቅርቡ ሥራ ላይ የሚውለው የኢነርጂ ፖሊሲ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ተደራሽነት ከማሳደግ አኳያ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው  በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ተቋማትና ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአስር ዓመት የልማት ዕቅዷ ልታከናውናቸው ካቀደቻቸው ተግባራት መካከል የኢኖቬሽን እና ኢንፎርሜሽን ሥራዎች ግንባር ቀደም እንደሆኑ ጠቅሰዋል::ዓለም የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ሒደት ውስጥ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ፍጆታን ከመቀነስ አኳያ ሚናቸው የጎላ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል።

የትራስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርሆ ሁሴን በበኩላቸው ታዳሽ፣ ተደራሽ፣ የተቀናጀ እና የደንበኞቹን ፍላጎት የሚያረካ እንዲሁም ለአካባቢ ተስማሚና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የትራንስፖርት ሥርዓት መዘርጋት የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የአስር  ዓመት ዋነኛ የልማት ግብ መሆኑን ተናግረዋል።በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የነዳጅ ብክነትን ከመቀነስ ባሻገር የካርበን ልቀትን መቆጣጠር እንዲያመች የታክስ ቅነሳ እና ማበረታቻዎችን በማድረግ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚታይ ለውጥ ማስመዝገብ እንደተቻለ አቶ በርሆ ገልፀዋል።

የካርዲናል ኢንደስትሪያል ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሊሊያ ኃይሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን በሀገር ውስጥ ለመጀመር ስለተደረገው ቅድመ ዝግጅት እና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ስለታቀደው ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።በይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የተቋማት ተወካዮች እና የሚዲያ አካላት ተሳትፈዋል።

“ከካርቦን ልቀት የፀዳ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል!”

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

2 × 5 =