ለኢትዮ – ኤሌክትሪክ የእግርኳስ ክለብ የዕውቅና እና ሽልማት መርሐግብር ተካሔደ

Published by corporate communication on

የኢትዮ- ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ  የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ተከትሎ ትናንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል የዕውቅና እና ሽልማት መርሐግብር ተካሒዷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ጫላ አማን ክለቡ ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም መመለሱ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

ክለቡ በቀጣይ ዓመት ጠንካራና ፈታኝ የውድድር ጊዜ እንደሚጠብቀው የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ  ለውጤታማ ጉዞው ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መጀመር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሁለቱ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች፣ የስፖርት ማህበሩ አባላት እንዲሁም መላው የስፖርት ቤተሰብ ለክለቡ ስኬታማነት ያደረጉት አስተዋጽኦ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን አውስተው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በ1953 ዓ.ም የተመሰረተው  የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ በአሁኑ ሰዓት ከ337 በላይ ስፖርተኞችን በተለያዩ ዘርፎች እያሰለጠነ እንደሚገኝ አቶ ጫላ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው እግር ኳስ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ መገንባት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ክለቡ ዳግም ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መመለሱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ክለቡ በቀጣዩ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪ ለመሆን ትልቅ የቤት ሥራ ስለሚጠብቀው ከወዲሁ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

በመርሐ-ግብሩ ለክለቡ ውጤት ማደግ አስተዋፅኦ ላደረጉ ተጨዋቾችና የስፖርት ክለቡ አባላት ዋንጫና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

ቡድኑ አንድ ጨዋታ እየቀረው ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀል በመቻሉ 11 ሚሊዮን ብር  ለተጨዋጮችና ድጋፍ ሰጪ አባላትም ተበርክቷል።

የስፖርት ክለቡ ውጤት እንዲያመጣ የክትትልና ድጋፍ  አስተዋፅኦ ላደረጉት የሁለቱ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችም ሽልማት ተሰጥቷል።

ክለቡ በ2014 ዓ.ም የብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን ሆኖ ያገኘውን ዋንጫ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኙና ፕሬዝዳንቱ በጋራ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚና ለስፖርት ክለቡ ጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ አቶ ሽፈራው ተሊላ አስረክበዋል።

በዕውቅና እና ሽልማት መርሐግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ እና የከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮ- ኤሌክትሪክ የእግር ኳስ ክለብ ከ4 ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ድጋሚ ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ማደጉን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

eight + thirteen =