ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሠራተኞችና የፀጥታ አካላት 40 ሰንጋዎች በስጦታ ተበረከተ

የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሠራተኞችንና የፀጥታ አካላትን በስፍራው በመገኘት አበረታቱ።
የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት በሙሉ ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ያላቸውን አድናቆት በመግለፅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደተናገሩት የአባይ ተፋሰስን ለመጠበቅ ክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ላይ በንቃት ተሳትፎ አድርጓል።
ለግድቡ ግንባታም እስካሁን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሊቱ በስኬት በመጠናቀቁም የአማራ ክልል ህዝብና መንግስት መደሰቱን ተናግረዋል።
የክልሉ ድጋፍም እስከ ግድቡ ፍፃሜ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የቤኑሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ለውጡን በየጊዜው ሲከታተሉ መቆየታቸውን ጠቅሰው የመጀመሪያ ዙር ሙሊቱ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
ይህንን ስኬት ከአማራ ክልል አቻቸው ጋር በመጎብኘት የፕሮጀክቱን ሠራተኞች ለማበረታታት በስፍራው መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ከርዕሳነ መስተዳድሮቹ ጋር ግድቡን የጎበኙትና በአባይ መነሻ ሰከላ የተወለዱት ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ለፕሮጀክቱ ሠራተኞች፣ ግድቡን ቀን ከሌት ለሚጠብቁ ለመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ አባላት አጋርነታቸውን ለመግለፅ 40 ሰንጋዎች በስጦታ አበርክተዋል።
አቶ በላይነህ ክንዴ እስካሁን ድረስ ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ቦንድ በመግዛት የሚታወቁ ሀገር ወዳድ ባለሀብት ሲሆኑ ለሀገሬ ሀብቴን ብቻ ሳይሆን ነፍሴን ጭምር እሰጣለው በሚል አገላለፃቸው ይታወቃሉ።
በጉብኝቱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ ደሚቱ ሀምቢሳ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ ተገኝን ጨምሮ የፌደራልና የክልል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
0 Comments