ለቁፋሮ ከሚያገለግሉ ሁለት የጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽኖች መካከል የአንድ ማሽን ተከላ ተጠናቋል

Published by corporate communication on

የአሉቶ የከርሰ ምድር እንፋሎት ጉድጓድ ቁፋሮ ለማካሄድ ከሚያስፈልጉት ሁለት የቁፋሮ ማሽኖች መካከል የአንዱ ማሽን ተከላ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአሉቶ ከርሰ ምድር እንፋሎት ፕሮጀክት አስታውቋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሳይት መሐንዲስ አቶ መሳይ ፍቃዱ እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት የሁለተኛው ማሽን ተከላም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ማሽኖቹ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን ያሟሉና ከ2 እስከ 2 ነጥብ 5 ኪ.ሜ ጥልቀት መቆፈር የሚያስችል አቅም እንዳላቸውና 350 ቶን ያህል ክብደት የመሳብ ወይም የመሸከም አቅም ያላቸው መሆኑን አቶ መሳይ ተናግረዋል፡፡

ከማሽን ተከላው ጎን ለጎን ለጉድጓድ ቁፋሮ የሚያገለግሉ እያንዳንዳቸው 4 ሚሊዮን ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት የውሃ ታንከሮች ገጠማ እና የውሃ መስመር ዝርጋታ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የውሃ መስመር ዝርጋታው እንደተጠናቀቀ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራው በይፋ እንደሚጀመርም ነው ያስታወቁት፡፡

የፕሮጀክቱ የሠው ኃይል አስተዳደር ባለሙያ አቶ ወርቁ ዱቄ በበኩላቸው በእስካሁኑ ሒደት ከ100 በላይ ኢትዮጵያዊያን በፕሮጀክቱ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልፀዋል፡፡

የቻይናው ኬሩይ /KERUI/ ኩባንያ የመቆፈሪያ ማሽኑን አምርቶ የገጠማ ስራውን በማከናወን ላይ ሲሆን የኬንያው ኬንጀን /KENJEN/ እና የቻይናው ኬሩይ ኦይል ፊልድ /KERUI Oil field/ ኩባንያዎች ደግሞ የጉድጓድ ቁፋሮውን ያከናውናሉ፡፡

የአሉቶ የከርሰ ምድር እንፋሎት ፕሮጀክት ከምድር በሚወጣ ተፈጥሯዊ እንፋሎት አማካኝነት 70 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ያለመ ነው፡፡

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

twenty + thirteen =