ለሠራተኞች የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የሚሰጠው በሚኖራቸው አፈፃፀም መሠረት ይሆናል ተባለ

Published by corporate communication on

የውጤት ተኮር የአፈፃፀም ስርዓት መዘርጋት ውጤታማ ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ የፐርፎርማንስ ማኔጅመንት እና ሪዋርድ ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው በውጤት ተኮር የአፈፃፀም ስርዓት  ( performance Management) ዙሪያ በትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ስራ አስፈፃሚ ስር ለሚገኙ የመምሪያ ኃላፊዎች እና ስራ አስኪያጆች የ3 ቀን ስልጠና ሰጥቷል።

የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ አእምሮ  እንደገለፁት ስልጠናው በተቋሙ የተዘረጋውን የውጤት ተኮር የምዘና ስርዓት ሁሉም የስራ መሪና ሠራተኛ ከተቋሙ ስትራቴጂ፣ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴቶች ጋር በማያያዝ እንዲፈጽም ለማድረግ ያግዛል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ የምዘና ሥርዓቱ ስርዓቱ ሠራተኞች በአፈፃፀማቸው ልክ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋትና ወጥነት ያለው የሥራ አፈፃፀም ምዘና ለማካሄድ ያገለግላል።

የውጤት ተኮር የአፈፃፀም ስርዓት መመሪያ  በ2011ዓ.ም ወጥቶ የነበረ ሲሆን በአተገባበር ግን ልዩነቶች እንደታዩበት ነው ሥራ አስኪያጁ ያስታወቁት።

በአሁኑ ሰዓት ግን የሠራተኞችን ጥቅማ ጥቅም በመመሪያው መሠረት እንዲፈፀም ለማድረግ እየተሰራ በመሆኑ ሠራተኛው ይህን ተገንዝቦ አፈፃፀሙን እንዲያሻሽል፣ ቅሬታ የቀነሰ ወይም የማይኖርበት ስርዓት ለመዘርጋትና የተቋሙን ግብ ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ከስልጠናው ጎን ለጎን በውጤት ተኮር የአፈፃፀም ስርዓት ዙሪያ ተሳታፊዎች በየክፍላቸው የነበሩ ችግሮችን አቅርበው ውይይት የተካሄደ ሲሆን ይህም በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት እንደሚያግዝ ነው የተገለፀው።

የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች የውጤት ተኮር የአፈፃፀም ስርዓት መመሪያውን ቢተገብሩ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደሚችሉ እና ባከናወኑት ተግባር ልክ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማመን ለተግባራዊነቱ በትብብር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሠው ሃብት ልማት መምሪያ ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው ስልጠናው የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ የሚገኝበትና የተነሱ ሃሳቦችን በመያዝ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

ከስልጠናው የተገኙ ሃሳቦችን በመያዝ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት መዘጋጀት እና ለመመሪያው መተግበር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እስከ አሁን ሪጅኖች የሠራተኞችን የሥራ አፈፃፀም መረጃዎችን በመላክ በኩል የተለያዩ ክፍተቶች እንደነበሩባቸውም  ኃላፊው አስታውሰው በቀጣይ ለሠራተኞች የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች  የሚሰጠው ከሥራ ክፍላቸው በሚላከው አፈፃፀም  መሠረት በመሆኑ ሪጅኖች የሠራተኞቻቸውን የአፈፃፀም  መረጃ በወቅቱ መላክ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሠራተኞችም መረጃቸው በወቅቱ መላኩን ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው የተባለው።

የትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሃብታሙ ውቤ በበኩላቸው ስልጠናው የተቋሙን ግብ ለማሳካትና ሠራተኛው ተቋሙ በሚተገብራቸው አሠራሮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንድኖረው ለማድረግ ፉይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የውጤት ተኮር አፈፃፀም ስርዓትን በተቋሙ ወጥ በሆነ መልኩ ለመተግበር የሥራ መሪዎች የሠራተኞችን አፈፃፀም ሲሞሉ የአፈፃፀም መለኪያዎችን መሠረት በማድረግ እና ፍትሃዊነትን በተላበሰ መልኩ ለማከናወን ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ሥራ አስፈፃሚው  አሳስበዋል።

በስልጠናው ላይ 40 የሚሆኑ በትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ስር የሚገኙ የመምሪያ ዳይሬክተሮችና ሥራ አስኪያጆች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ለሌሎች የስራ ክፍሎች ተመሳሳይ ስልጠና ለመስጠት  እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ከፐርፎርማንስና ሪዋርድ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

Categories: ዜና

0 Comments

Leave a Reply

Avatar placeholder

Your email address will not be published.

two × three =