ሃገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋምን በከፍተኛ ሁኔታ እንደለወጠው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፁ

Published by corporate communication Editor on

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከመጋቢት እስከ መጋቢት በሚል መሪ ቃል በራስ ሆቴል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ለተገኙ የሚዲያ አባላት ማብራሪያ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ እንደተናገሩት በሃገር አቀፍ ደረጃ እየመጣ ያለው ለውጥ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ላይ አወንታዊ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ለውጡ የተቋሙ አመራሮች ሙያዊ ብቃታቸውን ተጠቅመው ተልዕኳቸውን እንዲያስፈፅሙ ዕድል ያገኙበት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በዚህም ተቋሙ በፍጥነት ለውጥ እንዲያመጣ ትርጉም ያላቸው ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ እና የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክቶች የነበሩባቸው ችግሮች ተፈተው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉ የለውጡ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች ፕሮጀክቶችም በዕቅዳቸው መሠረት እንዲከናወኑ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በአዲሱ አደረጃጀቱ የትኩረት አቅጣጫውን ወደ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ቀይሯል ያሉት ዶ/ር አብርሃም በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ እንዳሉ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኢነርጂ ሴክተር የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ እንዲሰራ እንደ ሃገር አቅጣጫ ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት ዶ/ር አብርሃም በተቋሙ ቦርድ ፀድቀው ወደ ፕሮጀክት እየተቀየሩ ያሉ 13 ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ በአብዛኛው በውሃ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ከንፋስ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ ሥራዎች ተሰርተዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው የፀሐይ እና የምድር እንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ደግሞ በግል አልሚዎች ሊገነቡ የታሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር አብርሃም እንደተናገሩት የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የካሳ ክፍያ በወቅቱ ሊከፈል ባለመቻሉ ለ3 ዓመታት ያህል ግድቡ ውሃ ሳይዝ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ቢሆንም ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር የጋራ ምክክሮች በማድረግ ተቋሙ 2.9 ቢሊዬን ብር የካሳ ክፍያ እንዲከፍል፤ ነዋሪው ደግሞ የምንጣሮ ሥራዎችን እንዲያከናውን በመስማማት ግድቡ ውሃ እንዲይዝ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ የሚያከናውናቸው አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች በብድር እየተገነቡ የቆዩ መሆናቸውን ያወሱት ዶ/ር አብርሃም ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት የወጪ መጠኑን እየቀነሰና ገቢውን እያሳደገ በመሄዱ ምክንያት የፕሮጀክቶችን ወጪ በራሱ እየሸፈነ የመጣበት ሂደት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ የባህርዳር- ወልዲያ- ኮምቦልቻ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ፣ የአዳማ 2 የማከፋፈያ ኔትወርክ እና የተጨማሪ ትራንስፎርመሮችን ግዥ በራስ የፋይናንስ ወጪ ለመሸፈን ሥራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ዶ/ር አብርሃም ገልፀዋል፡፡

መጋቢት 26/2011 ዓ.ም

Categories: ዜና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

seventeen − 4 =

Facebook